Logo
Print this page

ቃል አቀባይነት

ቃል አቀባይነት

ሰሞኑን በነበረዉ የአሜሪካ የበጀት ክርክርና ቀዉስ ምክንያት በተደጋጋሚ መገናኛ ብዙሃን ብቅ ይሉ የነበሩ ዋና ሰዉ ጄይ ካርኔይ ይባላሉ። ሥራቸዉ የቤተ መንግሥት ቃል አቀባይነት (Whitehouse press secretary) ነዉ። ባጭሩ የፕሬዝዳንቱና የመንግሥታቸዉ “አፍ” (አፈ-ንጉሥ) ናቸዉ። ከዚህ የተነሳ ሲናገሩ ልብ ብላችሁ ከሆነ የሚያንጸባርቁት የራሳቸዉን ስሜትና አስተሳሰብ ሳይሆን የፕሬዝዳንቱን ነዉ። የሚናገሩት ተደጋጋሚ ሐረግ፡- “በፕሬዝዳንቱ እምነት”፤ “የፕሬዝዳንቱ አሳብ”  የምትል ናት። በዚያች “የንጉሥ መድረክ” ላይ የወደዱትን ሊሆኑ፣ የተሰማቸዉን ሊናገሩ አይችሉም። የቆሙት ንጉሥና መንግሥቱን ወክለዉ እንጂ የተሰማቸዉን ለመሆን አይደለምና።

የእኝህ ሰዉ ሥራ የእኔንና የብዙ አገልጋዮችን ጥሪ አስታወሰኝ። ጥሪያችን ልክ እንደሳቸዉ ነዉ፡- ንጉሡን እግዚአብሔር በመወከል የእርሱን አሳብና የመንግሥቱን አቋም ማንጸባረቅ ብቻ። “በእግዚአብሔር ፊት በሕያዋንና በሙታን ሊፈርድ ባለዉ በኢየሱስ ክርስቶስ ፊት፤ በመገለጡና በመንግሥቱም እመክርሃለሁ ቃሉን ስበክ… (2ጢሞ 4፡1-2)። ስለሆነም የመሰለንን፣ ምኞታችንን፣ የአድማጭ ፍላጎትንና ለእኛ ከብር የሚያመጣን ነገር ሁሉ ልንናገር አልተፈቀደልንም። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር አንዳንድ ነቢያትን “…ዉሸት…በስሜ ይናገራሉ…አላኳቸዉም፣ አላዘዝኳቸዉም አልተናገርኳቸዉም [ይልቁንም] የልባቸዉን ሽንገላ ይሰብኩላችኋል …” በማለት ይወቅሳል (ኤር 14፡14)። እንደዚህ ያሉ በንጉሡ ስም የራሳቸዉን ልብ የሚናገሩ ቃል አቀባዮች ታላቅ ቁጣና ፍርድ እንደሚጠብቃቸዉ ይናገራል (ቁ.15)። 

ቃል አቀባይነት እጅግ ክቡር ሥራ ነዉ! ንጉሥን ወክሎ ከመቆም የበለጠ ክቡር ሥራ ምን አለ? የንጉሡ እግዚአብሔር ሥልጣንና ኃይል አብሮን ይሆናል፣ ይሠራል! ነገር ግን ቃል አቀባይነት ደግሞ እጅግ የሚያስፈራ ሥራ ነዉ። የንጉሡን አሳብ (ቃሉን) በጥንቃቄ መረዳትና እርሱን ብቻ ለማንጸባረቅ መጨከን ያስፈልገናል። 

የንጉሥ አፍ የሆናችሁ ጓደኞቼ በዚህ የመጨረሻ ዘመን ንጉሡና መንግሥቱ እንዲከበሩ በምንቆምባቸዉ ቦታዎች ሁሉ አሳቡን እናገልግል። እዉነተኛ መንፈሳዊ ሥልጣን የሚመነጨዉ ንጉሡን በትክክል በመወከል እንጂ በራሳችን ጥበብ አይደለም። የሚመጡት የሳምንት መጨረሻ ቀናት፤ ከዚያም በኋላ እስኪመጣ ድረስ ይህን ለማድረግ የጨከነ መንፈስ ይስጠን። 

Mamusha Fenta

Mamusha Fenta is a Bible expositor and conference speaker residing in Addis Ababa, Ethiopia.

Website: www.mamushafenta.com/
mamushafenta.com © All rights reserved. Website Design @ BEKI Square