Mamusha Fenta

Mamusha Fenta

Mamusha Fenta is a Bible expositor and conference speaker residing in Addis Ababa, Ethiopia.

Website URL: http://www.mamushafenta.com/

ከአምና…ዘንድሮ

ሩቅ መንገድ ለመሔድ ተነስተን ስንጀምረው የሚደረስ አይመስልም። በመንገዳችን ዳር የተተከሉ የርቀት አመልካቾችም በጉዟችን ጅማሬ ላይ የሚያሳዩን ባለ ሦስትና አራት አሀዝ የኪሎ ሜትር ወይም ማይል ቁጥር ቶሎ መድረስ ለሚፈልግ መንገደኛ አታካች ናቸው። 

አንድ ሐቅ ግን ግልጽ ነው። አንድ ኪሎ ሜትር በነዳን ቁጥር ከሚቀረን ረጅሙ ርቀት ወስጥ አንድ ተቀንሷል። በሌላ አገላለጽ፡- ቅድም ከነበርንበት ርቀት በአንድ ኪሎ ሜትር  ወደ ፍጻሜያችን ተጠግተናል። ወደፊት በሔድን ቁጥር መድረሻችን ቀርቧል ማለት ነው።

ብዙ ጊዜ ባናስተውለውም ዘመንም እንዲሁ ነው። አንድ ዘመን በተጨመረልን ቁጥር ወደ ፍጻሜያችን በአንድ ዘመን ቀርበናል ማለት ነው። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ትላንት፣ ዛሬ፣ አምና፣ ዘንድሮ እያልን ስንቆጥር ወደ መጨረሻዉ (ወደ መዳናችን) እየተጠጋን ነው:- “ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና” ይላል (ሮሜ 13፡11)።  ደግሞም “…የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል” (1ጴጥ 4፡7) ብሎ ያሳስበናል።

በርግጥ ይህ እውነት ተዘጋጅተው ለሚኖሩ የሚያናውጥ ወይም አስደንጋጭ ሊሆን አይገባም (2ተሰ 2፡12)። ነገር ግን በማቴ 25 ላይ እንደ ተጠቀሱት በደንብ እስከ መጨረሻ ያልተዘጋጁ አምስቱ ሙሽራ ጠባቂ ቆነጃጅት የማንቂያ ደወል ነው። እንቅልፍ እንቅልፍ ባለን ጊዜ ማሰብ ያለብን እውነት ከትላንት ይልቅ ዛሬ እየተጠጋን መሆናችንን ነው። የማንቀላፋትና የለዘብተኝነት ዘመን አይደለም።

በአገራችን ዘመን አቆጣጠር አዲስ አመት ልንቀበል ነው። ነገ ‘ዘንድሮ’ ይሆንና ዛሬ ደግሞ ‘አምና’ ይባላል። የሕይወት ዘመን መቁጠሪያችን አንድ አመት ወደ ፍጻሜያችን መጠጋታችንን ታበስራለች። ቀን መቁጠሪያው በአንድ አመት በጨመረ ቁጥር መጨረሻው በአንድ አመት መቅረቡን መገንዘብ ለብዙዎቻችን አዳጋች አይመስለኝም። እንግዲያውስ አዲሱን አመት ስናከብር ከአምና ይልቅ ዘንድሮ ወደ ፍጻሜው መጠጋታችንን እያሰብን ይሁን። ስለሆነም በደስታ፣ በናፍቆትና በንቃት የበለጠ የምንዘጋጅበት ዘመን መለወጫ ይሁንልን።

ከአምና ይልቅ ዘንድሮ መዳናችን ቀርቧል- እንግዲህ እንንቃ!

 

መልካም አዲስ ዓመት!

Read more...

የክረምት ትዉስታ

ክረምት ከዝናቡ ጋር ብዙ ትውስታን ይዞ ይመጣል ይባላል። ለእኔ ሐምሌ በመጣ ቁጥር በላያችን ላይ የሚያንዣብበው ጥቁር ደመናና አየሩን እየሰነጠቀ የሚወርደው ዝናብ የሚያስታውሰኝ የተወለድኩባትን ቀን ነው። የተወለድኩት የዛሬ 27 ዓመት በዚህ ሰሞን ነበር። ቀኑ ደግሞ አንድ ቡሩክ ደመናማ የእሁድ ከሰዓት በኋላ። እያንዳንዱን የልደቴን ክስተት ሁልጊዜ እንደ ትላንት እያስታወስኩ እገረማለሁ፤ በተለይ ደግሞ ሐምሌ በመጣ ቁጥር። 

አንባቢዎቼን ግራ ማጋባቴ ገብቶኛል፤ ይቅርታ እጠይቃለሁ! የላይኛው አንቀጽ አንዳንዶቻችሁን ፈገግ ቢያሰኝም፤ ለብዙዎቻችሁ ወዳጆቼ ግን ጥያቄ መጫሩ አልቀረም፡- “ደግሞ ሰው የተወለደበትን ቀን ያስታውሳል ልትለን ነው? አንተን ደግሞ አናውቅህምና ነው እድሜህን ጎምደህ 27 ነው የምትለን?”  የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው።

በመጠየቃችሁ አልፈርድም ግን ስለ ሁለተኛው ልደቴ እያወራሁ መሆኑን ከነገርኳችሁ አይበቃም? ቅዱስ መጽሐፍ አንድ ጊዜ ከስጋ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዳግመኛ ከመንፈስ እንደምንወለድ ይነግረናል። በመንፈስ መወለድ ማለት ሐጢያተኛ መሆናችንን ተገንዝበን፤ ራሳችንንም ከአምላክ ፍርድ የምናድንበት ሌላ መንገድ እንደሌለ ተረድተን ክርስቶስን ስናምን፤ በመንፈሱ ወደልባችን ገብቶ የሚሰጠን የሕይወት ለውጥ ማለት ነው። 

በእርግጥ በጥሩ ሐይማኖታዊ ምግባር በማደጌ ስለ እግዚአብሔር ትንሿ አንጎሌ የቻለችውን ያህል አውቅ ነበር። ግን ልደብቀው የማልችለው ሐቅ እስከዚያች ቀን ድረስ በግል ቅዱስ ቃሉን አይቼም፣ አንብቤም አላውቅም። የራሴን ውሳኔ አድርጌም የግል (የአባትና ልጅ አይነት) ግንኙነት ከእግዚአብሔር ጋራ አልነበረኝም።

የዚያች ቡሩክ ክረምት ሰሞን ክንፈ ከሚባል ባለውለታዬ ጋር ተዋወቅን። ትውውቃችን የአጭር ጊዜ ቢሆንም ብዙ ሳንግባባ አልቀረንም። ከከተማችን እንግዳ ጋር መሰናበቻችን ከሆነችው የእሁዷ ከሰአት በኋላ በፊትም ይህ ነው የሚባል ሐይማኖታዊ ወሬ አልነበረንም። በዚያች እለት ግን የሚጢጢ ልቤን ትልቅ ትዕቢት የምትፈታተን “መጽሐፍ ቅዱስ አንብበህ ታውቃለህ?” በምትል ጥያቄ ጀምሮ፤ ትዕቢቴን ታግሶ፤ ሰምቻቸው የማላውቃቸውን ወርቃማ ቃላት ለመጀመሪያ ጊዜ ካየሁት ባለ ጥቁር ሽፋን መጽሐፍ ቅዱሱ ያነብልኝ ጀመር። እንደዚህ ሲነበብ ከዚያ በፊት ሰምቼ አላውቅም፡- 

“ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ” (ሮሜ3፡ 23-24)

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና… በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።” (ዮሐ 3፡ 16 እና 18)

“እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” (ዮሐ 14፡6)

የሚሉትንና የመሳሰሉትን ግሩም የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች ያለ ብዙ ተጨማሪ ማብራሪያ አንብቦ (በልቡ ሳይጸልይልኝ አልቀረም) ከክንፈ ጋር ተሰነባበትን። ወደቤቴ ገብቼ ለመተኛት ከሞከርኩባት ሰዓት ጀምሮ ግን ሌላ ልገልጸው የማልችለው የማይታይ ኃይል ሥራውን ጀመረ። ቀን የተነበቡልኝን ጥቅሶች ቃል በቃል ወደልቤ ያመጣቸው ጀመር (ሌላ ኃይል እንጂ እኔ በምን አቅሜ ላስታውሳቸው እችላለሁ?) ላለመቀበል ስታገል፤ ላለመካድም ሳልችል በተዳከመ ማንነት ነበር በማለዳ ወደ ክንፈ ዘንድ የሔድኩት። ክንፈም በፈገግታ የሌሊቱ ኃይል የመንፈስ ቅዱስ ሥራ መሆኑን አብስሮኝ፤ ስለ ዳግም ልደት ነግሮኝ እኔም እጆቼን ዘርግቼ መድሐኒቴን የተቀበልኩባት ቀን ነች ያች ቀን። አዲስ ሰው የሆንኩባት፤ ፍጹም ባልሆንም ግን ለመሆን የሚታገል ማንነት ያገኘሁባት የተባረከች ቀን!!!

የሕይወቴን ትላንት፤ ዛሬና ነገ በተለየ ሁኔታ እንድመለከት የሆንኩት በዚያች ቀን ምክንያት ነው። ትላንትን አስመልክቶ ከማህጸን የጀመረው ኃጢያቴ መደምሰሱን ማወቄ ነጻነትን ሰጠኝ (ሮሜ 8፡1 “በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም።”) ዛሬን በተመለከተ አዲስና ከፍ ያለ የመኖሬን ዓላማ ጨበጥኩ። መኖር የዚህን ዓለም የኑሮ ጣጣ ለማሟላት ከመሮጥ ባለፈ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል የሚደረግ ግስጋሴ እንደሆነ የገባኝም ያን ጊዜ ነው (ሮሜ 8፡29 “አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና።” ነገዬንስ ቢሆን ወዴት እንደምሔድ ዋስትናዬን የያዝሁት ከዚያች እለት ጀምሮ አይደለም ወይ? (1ዮሐ 5፡ 13 “የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ።”) ባጭሩ ከአምላኬ፤ ከራሴና ከሌሎች ወገኖቼ ጋር ታረቅሁ።

እንግዲህ በክረምቱ እንዲህ ባለ የትላንት ትውስታና የዛሬ ደስታ ውስጥ እገኛለሁ። ስለዚያች ቀን ጌታን እባርካለሁ። በሕይወቱ ተወራርዶ ወደዚህ ብርሃን የመራኝን ክንፈን ጌታ ብድራቱን ይክፈል እላለሁ። “በማዳንህ ደስ ይለናል” (መዝ 20፡5)

Read more...

“ድምጽ ነኝ!”

“አንተ ማን ነህ?” ቢሉት ማዕረጉን ፍለጋ

 ሰባኪዉ ዝም ጭጭ መልስ የለም እርሱ ጋ

“በል ባክህ ንገረን

ደግሞ እንቸኩላለን

ለሚጠባበቁን ወሬ እናደርሳለን፤

እንዲህ የሆነ እንደሁ ዝናህም ይወጣል

አገር ጉድ እያለ በክብር ያጅብሃል።”

ጠብ የሚል ሲጠፋ የሚደረድረዉ

የማዕረግ አይነት የሚከናነበዉ

እንደነበር ሲቆም በአንክሮ እያያቸዉ

አማራጭን ሰጡት እንዲመርጥላቸዉ።

“ክርስቶስ ነህ ኤልያስ ወይስ ነቢዩ ነህ? 

ምንስ ነዉ ማዕረግህ ማን ብለን እንጥራህ?

እባክህ ንገረን  ክብር  ደረጃህን

ስምና መለያ የሚመጥንህን”

ያን ጊዜ ከበደዉ መታገስ አቃተዉ

ማድመጥም አልቻለ እንኳን ሊደርበዉ

የሚጯጯሁትን ቀና ብሎ አየና

“ድምጽ ነኝ”! አላቸዉ እጅጉን ጮኸና

ያመጡትን ኮከብ የሚለጥፉትን

አራግፎ ከላዩ ሰዉ ሠራሽ ማዕረግን 

እንዲህ ሲል ቀጠለ ሰባኪው ጩኸቱን፡-

“ድምጽ ነኝ፣ ድምጽ ነኝ ያዉም የበረሀ

መንገድ የሚያቀና እንዲያልፍበት ዉሀ

እንደልቡ እንዲሔድ ሕይወት ሰጭዉ ጅረት 

ጥርጊያዉን አቅኝ ነኝ በሚሰጠኝ ምህረት 

በሉ አትነዝንዙኝ ማንነቴ ይህ ነው

ሌላ ምንም የለኝ ስለራሴ እምለዉ

ኋላዬ ያለዉ ግን ባለማዕረግ ነዉ

ከሰማይ የመጣዉ ክርስቶስ ጌታዬ 

ከሁሉ በላይ ነዉ።”

 

 (ዮሐ 1፧19-28)

 

 

Read more...

የማን ልደት ነዉ?

ሚሚዬ ልደቷ እየተቃረበ መምጣቱ ተደጋግሞ  ተነግሯታል። የዘንድሮዉ ለየት ባለ ሁኔታ በትልቅ ድግስ እንደሚከበርላት  ስለተነገራት ደስታዋ ወሰን አልነበረዉም። ወሬዋም አሳቧም እርሱዉ ሆኗል። ቤተሰብም ዝግጅቱን አጧጡፎታል።

እንዳይደርስ የለም ከብዙ ጥበቃ በኇላ ‘የሚሚዬ ልደት’ ቀን ደረሰ! በማለዳ የቀሰቀሳት የዝግጅቱ ግርግር ሲሆን ይህ ሁሉ ለእርሷ መሆኑ ገርሟት በደስታ ከአልጋዋ ዘልላ ወረደች።

እኩለ-ቀን ሲሆን ቤቱና ግቢዉ በታዳሚዉ ተሞላ። ፈንጠዝያዉ ቀጠለ፡- ይበላል፣ ይጠጣል፣ ይጨፈራል፣ ይሰከራል፣ ይሳቃል። በፈንጠዝያው መጨረሻ ግን ‘የሚሚዬ ልደት’ ማጠቃለያ ኬክ መቁረስ በመሆኑ አመሻሹ ላይ የልደቱ ኬክ  ሊቆረስ ተዘጋጀ። 

ሆኖም ግን በዚህ ወሳኝ ጊዜ ሁሉንም ሰዉ ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ተፈጠረ። ኬኩን ቆራሿ ሚሚዬ በአካባቢዉ ስትፈለግ ልትገኝ አልቻለችም። የሚያስገርመዉ ነገር በግርግሩ መሃል ባለልደቷ ለካ ተረስታ ነበር። ከጠዋት ጀምሮ ያስታወሳትም ያያትም ሰዉ አልነበረም። አሁን ግን ከመኝታ ቤቷ እስከሰፈር ድረስ ፍለጋዉ ቀጠለ።

ከብዙ ዉጣ ዉረድ ብሇላ ባለልደቷ ሚሚ ሰፈር ውስጥ ከሌሎች ልጆች ጋር እየተጫወተች ተገኘች። እንደዋና ባለጉዳይ ወግ ያለዉ ልብስ ያለበሳት እንኯ አልነበረም፤ የለበሰቻትም የሌሊት ልብስ አቧራ ለብሳለች። የሚሚዬ ወላጆች በቁጣ ተሞልተዉ “በልደትሽ ቀን አዋረድሽን!” የሚል የጩዀት ዝናብ ያወርዱባት ጀመር። ልጃቸዉ ያቀረበችዉን ብርቱ ጥያቄ ግን የሚመልሱበት የሞራል ብቃት አልነበራቸዉም።

የልጅ ዓይኖቿን ወደላይ እቅንታ እየተመለከተች፡- “እኔኮ ልደቱ የእኔ መስሎኝ ጠዋት በደስታ ነበር የነቃሁት። ትኩረት የሚሰጠኝና የሚያለብሰኝ ከማጣቴም በላይ የምታደርጉትን ሁሉ ዝም ብዬ ስመለከት ልደቱ የእናንተ መስሎኝ ነዉ ለመጫወት የወጣሁት። ለመሆኑ ልደቱ የማን ነዉ የእኔ ወይስ የእናንተ?” ለወላጆቿ ብቻ ሳይሆን በልጅ አመካኝተዉ ሲበሉ፣ ሲጠጡ ለዋሉ ‘አዋቂዎች’ ሁሉ ይቅርታ ከመጠየቅ  በቀር ሌላ መልስ መስጠት የቻለ አልነበረም። 

ይህን አፈታሪክ ያነሳሁት ለምን እንደሆነ ሳይገባችሁ አልቀረም። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ደርሷል። በመሆኑም ገበያዉ ሞቅ ማለት ጀምሯል። የልደት በዓል ከጊዜ ወደ ጊዜ ‘የኛ ብቻ’ እየሆነ መጥቷል። ከቤተክርስቲያናት ይልቅ ቤተመጠጦች የሚደምቁበት፤ የመብል የመጠጥ፣ የጭፈራና የሌሎችም ብዙ ’ራስ ማስደሰቻ’ ጊዜ አርገነዋል።

ባለልደቱ ተገልጦ “ለመሆኑ የማን ልደት ነዉ?” ቢለን መልስ መስጠት የምንችል ስንቶች እንሆን? የምናፍርስ?

ልደቱ የጌታችን የመድሐኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በመሆኑ እርሱ የሚከብርበት ሊሆን ይገባል። “መድሐኒት ተወልዶልናል” (ሉቃ 2፡11) የሚል ብስራት የሚያስተጋባበትና “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ” የሚል  ዜማ ወደላይ ወደርሱ የሚያርግበት ሊሆን ይገባል።

በሉ ተነሱ ልደቱን እናክብር! ግን አስታዉሱ ልደቱ የኢየሱስ ነዉ! ክብርም ለእርሱ ነዉ፩ መልካም ልደት ይሁንልን!

Read more...
Subscribe to this RSS feed

Log in or Sign up