የክረምት ትዉስታ

  • Read 5273 times
  • Print
  • Email

ክረምት ከዝናቡ ጋር ብዙ ትውስታን ይዞ ይመጣል ይባላል። ለእኔ ሐምሌ በመጣ ቁጥር በላያችን ላይ የሚያንዣብበው ጥቁር ደመናና አየሩን እየሰነጠቀ የሚወርደው ዝናብ የሚያስታውሰኝ የተወለድኩባትን ቀን ነው። የተወለድኩት የዛሬ 27 ዓመት በዚህ ሰሞን ነበር። ቀኑ ደግሞ አንድ ቡሩክ ደመናማ የእሁድ ከሰዓት በኋላ። እያንዳንዱን የልደቴን ክስተት ሁልጊዜ እንደ ትላንት እያስታወስኩ እገረማለሁ፤ በተለይ ደግሞ ሐምሌ በመጣ ቁጥር። 

አንባቢዎቼን ግራ ማጋባቴ ገብቶኛል፤ ይቅርታ እጠይቃለሁ! የላይኛው አንቀጽ አንዳንዶቻችሁን ፈገግ ቢያሰኝም፤ ለብዙዎቻችሁ ወዳጆቼ ግን ጥያቄ መጫሩ አልቀረም፡- “ደግሞ ሰው የተወለደበትን ቀን ያስታውሳል ልትለን ነው? አንተን ደግሞ አናውቅህምና ነው እድሜህን ጎምደህ 27 ነው የምትለን?”  የሚሉት ጥቂቶቹ ናቸው።

በመጠየቃችሁ አልፈርድም ግን ስለ ሁለተኛው ልደቴ እያወራሁ መሆኑን ከነገርኳችሁ አይበቃም? ቅዱስ መጽሐፍ አንድ ጊዜ ከስጋ ሌላ ጊዜ ደግሞ ዳግመኛ ከመንፈስ እንደምንወለድ ይነግረናል። በመንፈስ መወለድ ማለት ሐጢያተኛ መሆናችንን ተገንዝበን፤ ራሳችንንም ከአምላክ ፍርድ የምናድንበት ሌላ መንገድ እንደሌለ ተረድተን ክርስቶስን ስናምን፤ በመንፈሱ ወደልባችን ገብቶ የሚሰጠን የሕይወት ለውጥ ማለት ነው። 

በእርግጥ በጥሩ ሐይማኖታዊ ምግባር በማደጌ ስለ እግዚአብሔር ትንሿ አንጎሌ የቻለችውን ያህል አውቅ ነበር። ግን ልደብቀው የማልችለው ሐቅ እስከዚያች ቀን ድረስ በግል ቅዱስ ቃሉን አይቼም፣ አንብቤም አላውቅም። የራሴን ውሳኔ አድርጌም የግል (የአባትና ልጅ አይነት) ግንኙነት ከእግዚአብሔር ጋራ አልነበረኝም።

የዚያች ቡሩክ ክረምት ሰሞን ክንፈ ከሚባል ባለውለታዬ ጋር ተዋወቅን። ትውውቃችን የአጭር ጊዜ ቢሆንም ብዙ ሳንግባባ አልቀረንም። ከከተማችን እንግዳ ጋር መሰናበቻችን ከሆነችው የእሁዷ ከሰአት በኋላ በፊትም ይህ ነው የሚባል ሐይማኖታዊ ወሬ አልነበረንም። በዚያች እለት ግን የሚጢጢ ልቤን ትልቅ ትዕቢት የምትፈታተን “መጽሐፍ ቅዱስ አንብበህ ታውቃለህ?” በምትል ጥያቄ ጀምሮ፤ ትዕቢቴን ታግሶ፤ ሰምቻቸው የማላውቃቸውን ወርቃማ ቃላት ለመጀመሪያ ጊዜ ካየሁት ባለ ጥቁር ሽፋን መጽሐፍ ቅዱሱ ያነብልኝ ጀመር። እንደዚህ ሲነበብ ከዚያ በፊት ሰምቼ አላውቅም፡- 

“ሁሉ ኃጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔርም ክብር ጎድሏቸዋል፤ በኢየሱስ ክርስቶስም በሆነው ቤዛነት በኩል እንዲያው በጸጋው ይጸድቃሉ” (ሮሜ3፡ 23-24)

“በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና… በእርሱ የሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል።” (ዮሐ 3፡ 16 እና 18)

“እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” (ዮሐ 14፡6)

የሚሉትንና የመሳሰሉትን ግሩም የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች ያለ ብዙ ተጨማሪ ማብራሪያ አንብቦ (በልቡ ሳይጸልይልኝ አልቀረም) ከክንፈ ጋር ተሰነባበትን። ወደቤቴ ገብቼ ለመተኛት ከሞከርኩባት ሰዓት ጀምሮ ግን ሌላ ልገልጸው የማልችለው የማይታይ ኃይል ሥራውን ጀመረ። ቀን የተነበቡልኝን ጥቅሶች ቃል በቃል ወደልቤ ያመጣቸው ጀመር (ሌላ ኃይል እንጂ እኔ በምን አቅሜ ላስታውሳቸው እችላለሁ?) ላለመቀበል ስታገል፤ ላለመካድም ሳልችል በተዳከመ ማንነት ነበር በማለዳ ወደ ክንፈ ዘንድ የሔድኩት። ክንፈም በፈገግታ የሌሊቱ ኃይል የመንፈስ ቅዱስ ሥራ መሆኑን አብስሮኝ፤ ስለ ዳግም ልደት ነግሮኝ እኔም እጆቼን ዘርግቼ መድሐኒቴን የተቀበልኩባት ቀን ነች ያች ቀን። አዲስ ሰው የሆንኩባት፤ ፍጹም ባልሆንም ግን ለመሆን የሚታገል ማንነት ያገኘሁባት የተባረከች ቀን!!!

የሕይወቴን ትላንት፤ ዛሬና ነገ በተለየ ሁኔታ እንድመለከት የሆንኩት በዚያች ቀን ምክንያት ነው። ትላንትን አስመልክቶ ከማህጸን የጀመረው ኃጢያቴ መደምሰሱን ማወቄ ነጻነትን ሰጠኝ (ሮሜ 8፡1 “በክርስቶስ ኢየሱስ ላሉት አሁን ኩነኔ የለባቸውም።”) ዛሬን በተመለከተ አዲስና ከፍ ያለ የመኖሬን ዓላማ ጨበጥኩ። መኖር የዚህን ዓለም የኑሮ ጣጣ ለማሟላት ከመሮጥ ባለፈ ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል የሚደረግ ግስጋሴ እንደሆነ የገባኝም ያን ጊዜ ነው (ሮሜ 8፡29 “አስቀድሞ ያወቃቸው የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና።” ነገዬንስ ቢሆን ወዴት እንደምሔድ ዋስትናዬን የያዝሁት ከዚያች እለት ጀምሮ አይደለም ወይ? (1ዮሐ 5፡ 13 “የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ታውቁ ዘንድ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ለምታምኑ ይህን ጽፌላችኋለሁ።”) ባጭሩ ከአምላኬ፤ ከራሴና ከሌሎች ወገኖቼ ጋር ታረቅሁ።

እንግዲህ በክረምቱ እንዲህ ባለ የትላንት ትውስታና የዛሬ ደስታ ውስጥ እገኛለሁ። ስለዚያች ቀን ጌታን እባርካለሁ። በሕይወቱ ተወራርዶ ወደዚህ ብርሃን የመራኝን ክንፈን ጌታ ብድራቱን ይክፈል እላለሁ። “በማዳንህ ደስ ይለናል” (መዝ 20፡5)

Last modified onWednesday, 22 July 2015 08:50
Mamusha Fenta

Mamusha Fenta is a Bible expositor and conference speaker residing in Addis Ababa, Ethiopia.

Website: www.mamushafenta.com/

Leave a comment

Make sure you enter all the required information, indicated by an asterisk (*). HTML code is not allowed.

Log in or Sign up