ከአምና…ዘንድሮ

  • Read 4392 times
  • Print
  • Email

ሩቅ መንገድ ለመሔድ ተነስተን ስንጀምረው የሚደረስ አይመስልም። በመንገዳችን ዳር የተተከሉ የርቀት አመልካቾችም በጉዟችን ጅማሬ ላይ የሚያሳዩን ባለ ሦስትና አራት አሀዝ የኪሎ ሜትር ወይም ማይል ቁጥር ቶሎ መድረስ ለሚፈልግ መንገደኛ አታካች ናቸው። 

አንድ ሐቅ ግን ግልጽ ነው። አንድ ኪሎ ሜትር በነዳን ቁጥር ከሚቀረን ረጅሙ ርቀት ወስጥ አንድ ተቀንሷል። በሌላ አገላለጽ፡- ቅድም ከነበርንበት ርቀት በአንድ ኪሎ ሜትር  ወደ ፍጻሜያችን ተጠግተናል። ወደፊት በሔድን ቁጥር መድረሻችን ቀርቧል ማለት ነው።

ብዙ ጊዜ ባናስተውለውም ዘመንም እንዲሁ ነው። አንድ ዘመን በተጨመረልን ቁጥር ወደ ፍጻሜያችን በአንድ ዘመን ቀርበናል ማለት ነው። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን ትላንት፣ ዛሬ፣ አምና፣ ዘንድሮ እያልን ስንቆጥር ወደ መጨረሻዉ (ወደ መዳናችን) እየተጠጋን ነው:- “ካመንንበት ጊዜ ይልቅ መዳናችን ዛሬ ወደ እኛ ቀርቦአልና” ይላል (ሮሜ 13፡11)።  ደግሞም “…የነገር ሁሉ መጨረሻ ቀርቦአል” (1ጴጥ 4፡7) ብሎ ያሳስበናል።

በርግጥ ይህ እውነት ተዘጋጅተው ለሚኖሩ የሚያናውጥ ወይም አስደንጋጭ ሊሆን አይገባም (2ተሰ 2፡12)። ነገር ግን በማቴ 25 ላይ እንደ ተጠቀሱት በደንብ እስከ መጨረሻ ያልተዘጋጁ አምስቱ ሙሽራ ጠባቂ ቆነጃጅት የማንቂያ ደወል ነው። እንቅልፍ እንቅልፍ ባለን ጊዜ ማሰብ ያለብን እውነት ከትላንት ይልቅ ዛሬ እየተጠጋን መሆናችንን ነው። የማንቀላፋትና የለዘብተኝነት ዘመን አይደለም።

በአገራችን ዘመን አቆጣጠር አዲስ አመት ልንቀበል ነው። ነገ ‘ዘንድሮ’ ይሆንና ዛሬ ደግሞ ‘አምና’ ይባላል። የሕይወት ዘመን መቁጠሪያችን አንድ አመት ወደ ፍጻሜያችን መጠጋታችንን ታበስራለች። ቀን መቁጠሪያው በአንድ አመት በጨመረ ቁጥር መጨረሻው በአንድ አመት መቅረቡን መገንዘብ ለብዙዎቻችን አዳጋች አይመስለኝም። እንግዲያውስ አዲሱን አመት ስናከብር ከአምና ይልቅ ዘንድሮ ወደ ፍጻሜው መጠጋታችንን እያሰብን ይሁን። ስለሆነም በደስታ፣ በናፍቆትና በንቃት የበለጠ የምንዘጋጅበት ዘመን መለወጫ ይሁንልን።

ከአምና ይልቅ ዘንድሮ መዳናችን ቀርቧል- እንግዲህ እንንቃ!

 

መልካም አዲስ ዓመት!

Last modified onMonday, 14 September 2015 09:11
Mamusha Fenta

Mamusha Fenta is a Bible expositor and conference speaker residing in Addis Ababa, Ethiopia.

Website: www.mamushafenta.com/
More in this category: « የክረምት ትዉስታ

Leave a comment

Make sure you enter all the required information, indicated by an asterisk (*). HTML code is not allowed.

Log in or Sign up